Saturday, July 18, 2015

ቁዘማ፤ ከዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች ብይን በፊት

 በፍቃዱ ዘ ሃይሉ
‹‹ስድስት መሥመር ስጡኝ፣
በታላቅ ፀሐፊ ከተጻፈ ድርሰት፤
አላጣም ምክንያት፣
አንዳች እክል ስህተት፣
ያንን ሰው ወንጅዬው የማሰቅልበት፡፡››
‹‹ለምን እፅፋለሁ?››
ጆርጅ ኦርዌል ‹‹ገንዘብ ለማግኘት›› ከሚደረግ ጥረት ውጪ ጸሐፍት የሚጽፉባቸውን ‹‹አራት ትላልቅ መግፍኤዎችን›› እንደዘረዘረ አንድ መጽሐፍ ላይ አነበብኩ፡፡ እነዚህ ከተራ ጉራ (sheer Egoism) - ጎበዝ መስሎ ለመታየት፣ ስለራስ እንዲወራ፣ ወይም ከሞት በኋላ ለመታወስ ለመሳሰሉት ዒላማ፤ ለጥበባዊ ግብ (aesthetic enthusiasm) - ዋጋ የሚሰጡትንና ሰዎች እንዲሰሙት የሚፈልጉትን ነገር የማጋራት ጉጉት፤ ለታሪካዊ ጥቅም (historical impulse) - ስለታሪክ እውነቱን የመለየትና ለወደፊቱ የማስቀመጥ ግብ እና ለፖለቲካዊ ተግባር (Political purpose) - ዓለምን ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ የመግፋት ዒላማ የሚደረጉ የምኞት መጻፎች ናቸው፡፡
የእኔም የመጻፍ አባዜ (ልበለው?) ከእነዚህ ኦርዌል መግፍኤዎች አንዱ ወይም ከፊሉ ወይም ሁሉም ወይም ማንኛውም ሊሆን ይችላሉ፡፡ ወይም ደሞ ነብይ መኮንን በግጥም እንዳለው ‹‹ስለሚያመኝና መፃፍ ስለሚያክመኝ›› ይሆናል፡፡ እንድ ነገር ግን አምናለሁ፡፡ የቮልቴርን አፍ ተውሼ እምነቴን ልናገር:- "we can, by speech and pen, make men more enlightened and better." (በንግግር እና ብዕር ሰዎች የነቁና የተሻሉ እንዲሆኑ ማድረግ እንችላለን፡፡)
ማዕከላዊእያለሁ የገባሁት ቃል ቢቆጠር ኖሮ መርማሪዎቼን ‹‹ፍቱኝ እንጂ ሁለተኛ አይለምደኝም›› ብዬ ለምኛቸው ነበር፡፡ መጻፍ ነውአይለምደኝምያልኩት፡፡ ልክ እንደልጅነቴ! ያኔ እናቴ ስትገርፈኝ እል እንደነበረው፡፡ ለምን እንደሆነ እንጃ እየተገረፍኩ የገባሁትን ቃል ያኔም፣አሁንም ማክበር አይሆንልኝም፡፡ ይኸው አሁንም እየጻፍኩ ነው፡፡ ይሄንኛው ለአንባቢ ከበቃ የማረሚያ ቤት ፈታሾች ሲሳይ ከሆኑት ቁዘማዎቼ ተነጥሎ ዕድል ገጥሞታል ማለት ነው፡፡
"It takes Power to talk to Power" (‹ጉልቤን ለማናገር ጉልቤ መሆን ያሻልእንደማለት) ይል ነበር አሉ ሳተናው ማልኮም ኤክስ፡፡ እኔና ጓደኞቼ ግን አፈሙዙን በአፈ-ብዕር ለማናገር ሞክረናል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ታጋይ እያሉ ተስፋፅዮን መድኃንዬ(/) የተባሉ ኤርትራዊ ላሳተሙት Eritrea : dynamics of a national question መፅሐፍ የመልስ ምት ጽፈው ነበር፡፡ ተስፋጽዮንችግራችንን በሰላማዊ መንገድ እንፍታብለው በመጽሐፋቸው ሽፋን ገጽ ላይ በአፍጢሙ የተተከለ ጠብመንጃ (ከአበባ ጋር) በስዕል አስፍረው ነበር፡፡ አቶ መለስ በመልስ ምታቸው ‹‹ብረት ህዝቢ ኤርትራ ቁልቁል አፉ ኣይድፋእን›› ብለው አፈሙዟን ሽቅብ አቁመው ነፍስ ዘሩባት፡፡ የእሳቸው ትግል በአፈብዕርም፣ አፈሙዝም ነበር፡፡ አንደኛው ብቻ የሚገባቸው አይመስልም፡፡ ቁጭ ብዬ እየቆዘምኩ አስባለሁ፡፡ እንዳለመታደል (እንደመታደል) ሆኖ፣ ዛሬም፣ ከታሰርኩ ከአመት በኋላ የእርሳቸው ዓይነት ሌላኛው አማራጭ አይዋጥልኝም፡፡
የታሰርኩት በመጻፌ ነው፡፡ ዐቃቤ ሕግ ‹‹ይህ ሰው አሸባሪነው፤ የማሕረሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል›› ብሎ ሲከሰኝ ያቀረበብኝ ማስረጃ ጽሑፎቼን ነው፡፡ ዐቃቤ ሕጉን ክሰስልኝ ያሉት ሰዎች ጽሑፎቼን በጽሑፍ ለመመከት ከመሞከር ይልቅ እንደመፍትሔ የታያቸው እኔን ዝም ለማሰኘት መሞከር ነው፡፡ ስለሚችሉ፡፡ አልፎ፣ አልፎ . . . የተከሰስኩባቸውን ጽሑፎች እመለከታቸዋለሁ፡፡ ‹‹መሰለፍ እና መሰየፍ ›› የሚል ርዕስ አያለሁ፡፡ ያላለቀ ጽሑፍ ነው፡፡ ሕዝቦቹን የማያምን መንግስት ሕዝቦች በሰላማዊ መንገድ ሲሰለፉ ሰይፉን ይመዛል ይላል፡፡ መቼም ሲያነቡት አይከሱኝም እላለሁ፡፡ አንዳንዱ ጽሑፍ እኔን ለመክሰስ ሳይሆን ለመከላከል ክሴ ላይ የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ ሌሎቹን አነባለሁ፡፡ ‹‹80 ሚሊዮን እስከምንደርስ እንታገላለን ››ይላል፡፡ እንደ አምባገነኑ መንጌ ‹‹አንድ ጠመንጃ የሚል ተስፋ መቁረጥ አይነካካኝም›› ነው ነገሩ፡፡ ልዩነቱ የእኛ ትግል በብዕር ነው፡፡ 80 ሚሊዮን እኮ ሁላችንም ነን -እኛም፣ እንዲለወጡ የምንፈልጋቸው መሪዎቻችንም ተደምረን፡፡ ‹‹ድር ቢያብር ለአምባገነኖች ምናቸው ነው?›› የሚልም አለ (‹‹በሰገሌ ጊዜ›› ተጽፎ እኔም አንባቢዎቼም የረሳነው ጽሑፍ) ብዙዎቹ ማስረጃ የተባሉብኝ ጽሑፎች የተፃፉት ዞን ዘጠኝ ከመመስረቱ በፊት ነው፡፡ እውነት ግን ድር ቢያብር ለአምባገነኖች ምናቸው ነው? ‹‹አብዮት ወረት ነው›› የሚልና ሌሎችም አሉ፡፡ ሁሉም ግን ጽሑፎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ዞን ዘጠኝ ሲያደርጋቸው የነበሩ የብይነ መረብ ዘመቻዎች - ጋዜጣዊ መግለጫዎችም - የክሳቸን ማስረጃ ተብለዋል፡፡ ሕገ - መንግስቱ እንዲከበር ይጠይቃሉ፡፡
ያስከሰሱኝን ጽሑፎች ከጎኔ ለሚተኛው እስረኛ አስነበብኩት፡፡ ‹‹እንዴ፣ እንዴ . . . ›› አለ ገርሞት፡፡ ‹‹. . . ሁለት አመት ሙሉ መንግስት እንዴት ታገሳችሁ?›› የሕገ-መንግስታችንን አንቀጽ 29(ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት) አነበብኩለት፡፡ ‹‹እሱ እኮ ኢሕአዴግ አይውጠው ነገር አምልጦት የተናገረው ነገር ነው፤ አንተ አምልጦህ የገባኸው ቃል፣ ቆይቶ ግን የሚፀፅትህ የለም?›› አለኝ፡፡ ለአልጋ ጎረቤቴ ከዚህ በላይ ላስረዳው አልሞከርኩም፡፡ ‹‹በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት . . .›› የሚለው ተውሼ ያዋስኩትን ልቦለድ ነው፡፡ ባይረዳኝም እኔ እረዳዋለሁ፡፡
ለኔ መጻፍ መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው፡፡ የሚያስገድደኝ አንዳች ጎትጓች ኃይል ውስጤ አለ፤ ይህንን ለእሱ ነግሬ ማሳመን አልችልም፡፡ ለነገሩ ለሌሎችም ነግሬ ማሳመን እየከበደኝ ነው፡፡ ‹‹አንተ የመንግስታቸንን ባሕሪ እያወቅከው ለምን ተዳፈርክ?›› ይሉኛል ችግሩ ከጽሑፌ ሳይሆን ከመንግስታችን መሆኑን የሚረዱት ዘመድ ወዳጆቼ ሳይቀሩ፡፡ዝም ብሎ የመኖርን ጥበብግን አይነግሩኝም፡፡ዝምታነዋ ቋንቋቸው! የባቢሎን ግምብ መሐላችን ቆሟል፡፡
‹‹
ብዙኃን ይመውዑ›› ይባላል፡፡ብዙኃንስ ይፈርዱብኝ ይሆን?› ይላል ልቤ፡፡ ምክንያቱም ልቤ በፍሬድሪክ ኒቼ አባባል ያምናል፡- "There are no facts, but interpretations." (ሐቅ ብሎ ነገር የለም፣ አተረጓጎም እንጂ)፡፡ ወዳጄ እና አባሪዬ አቤል ዋበላ ሁሌ ይሞግተኛል፤ ‹‹ነጭ ወይም ጥቁር (‹‹መላጣ››) እውነት ነው ያለው›› እያለ፡፡ እኔ ግን ‹‹እውነት ግራጫ ነች›› ባይ ነኝ፡፡ ይቺን ግራጫ እውነት እኔ ጽፌያት ብዙኃን ሲቀበሏት ነው የማይፈርዱብኝ፡፡ እውነቴ አይታያቸው ይሆናል፤ እኔግን አልቆጭም፡፡ ምክንያቱም፣ በቁዘማዬ መግቢያ አካባቢ እንዳልኩት ‹‹ብዕር ሰዎች ያነቃል›› ብዬ አምኜ ጽፌያለሁ፡፡ ብዕር ሁለት አፈሙዝ እንዳለው ሽጉጥ ነው፡፡ ተኳሹንም፣ ዒላማውንም ይመታል፡፡
በብዛት የጻፍኩት ራሴን ለማሳመን ስፍጨረጨር እግረ መንገዴን መሰሎቼን ለማሳመን ነው፡፡ ዒላማዬን ስቼ ብሆን እንኳ እራሴን አልሳትኩም፡፡ ዒላማዬን መሳትም ቢሆን የተኳሹ ድክመት ላይሆን የችላል፡፡ እጓለ ገብረ ዮሐንስ እንዳሉት ‹‹ጎልማሳ ጦርም ሆነ ሽመል አርቆ ይወረውራል፤ ዒላማውን ሳይመታ ቢቀር ከክንዱ መድከም ብቻ ሳይሆን ኢላማውም ወላዋይነት ሊሆን ይችላል፡፡››
መንግስታችን በኦርዌሊያን ፈሊጥ ነው የሚመራው (‹ሚ› ጠብቆ በይም ላልቶ ቢነበብ ግዴለም)፡፡ የወደፊቱን ለመቆጣጠር፣ አሁንን አጥብቆ ይዟል (እንደ ነብር ጭራ)፣ ያለፈውን ባሻው መንገድ ይተረጉማል፡፡ ለዚህ ግቡ መገናኛ ብዙኃን አንድም የእሱ ድምጽ የገደል ማሚቶ እንዲሆኑ አሊያም እንዲጠፉ ነው ምኞቱ፡፡ የእኔና የጓደኞቼ ምኞት ደግሞ ተቃራኒው ነበር ቢያንስ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ አማራጭ ድምፅ መሆን ተመኝተን ነበር፡፡ ለአማራጭ ድምፅነት የሰጠነው የተጋነነ ዋጋ በበኩሌ ኢ-ምክንያታዊ አይመስለኝም፡፡ ግራጫ እያልኩ የማጣቅሳት እውነት የምትወለደው ‹‹ጫፍ አልባ በሆነ›› የነጭ እና ጥቁር እውነቶች ፍጭት ነው፡፡ አማራጭ ቀለም ባይኖር ኖሮ የቀለሙን ዓይነት መጥራትም (መሰየምም) አያስፈልግም ነበር፡፡
ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት መንግስታችን ኦርዌሊያን ነው፡፡ ታሪክና ትርክትን መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ ያንን የሚያደርገው ደግሞ አንድም በብዕር (መገናኛ ብዙኃንን በመቆጣጠር)፣ አንድም በኃይል (አማራጭ ድምፃችንን በማፈን) ነው፡፡ ወቅቱ ከምርጫ 97 ማግስት ወዲህ ብዙ ጋዜጠኞችና ጸሐፍት የታሰሩበትና የተሰደዱበት ነው፡፡ እኔና ጓደኞቼም የዚሁ ዘመቻ ሰለባ ሆነናል፡፡ የታሰርነው ምርጫ 2007ን ምክንያት በማድረግ እንደሆነ ይገመታል፡፡አሁን ምርጫው ገዢው ፓርቲ በሚፈልገው መልኩ ተጠናቋል፡፡ ዳኞች የአቃቤ ሕጉን ማስረጃዎች መርምረው ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 13 ቀን ቆርጠዋል፡፡ ብዙዎች ይጠየቁኛል፤ ‹‹ምን እንጠብቅ?››
ሌሎች ምን መጠበቅ እንዳለባቸው ለመንገር ቀርቶ እኔ ራሴ ምን መጠበቅ እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ የማውቀው ፍ/ቤቱ የሚወስነው ሳይሆን ለኔ(እና ጓደኞቼ) የሚገባንን ነው፡፡ ከነፃ በታች አያዋጣንም፡፡ ሆኖም ግን ሊሆን የማይገባው (ይሆናልና) ሆኖ ‹‹ጥፋተኛ›› ብንባልስ? መልሱን ከትልቅ ሰው አፍ ተንጠራርቼ እዋሳለሁ፡፡

‹‹የታህሳሱ ግርግር ›› በመባል የሚታወሰው የንጉሱ መፈንቅለ መንግስት እንደከሸፈ፣ ተሳታፊዎቹን የዳኙት ኖርዌያዊው ዳኛ ኤድቫርድ አምብሮ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ላይ የሞት ቅጣት ሲበይኑባቸው ጄኔራሉ እንዲህ ነበር ያሉት፡- ውሳኔያችሁ ላይ ይግባኝ የለኝም፡፡ ፍትሕ የነፈጋችሁኝ ይህ ክስ ባግባቡ እንዳልከላከል ስታደርጉኝ ገና ነው፡፡ ያላችሁትን አድርጌያለሁ ፣ ግን ጥፋተኛ አደለሁም፡፡ ጽሑፍ እንደማስረጃ አቅርበው ‹‹አሸባሪ›› ነህ ካሉኝ፣ ከዚህ (ከጄኔራል መንግስቱንግግር) በላይ የማስተባብልበት አፍ የለኝም፡፡
BefeQadu Z Hailu


No comments:

Post a Comment