Saturday, July 18, 2015

የዕለት ተዕለት ጥያቄዎቻችን

በናትናኤል ፈለቀ
Natnael Feleke
ለምን እጅግ አላስፈላጊ ዋጋ ታስከፍናለህ? አንተ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በምን ትለያለህ? በግል የደረሰብህ በደል የለ! አንተ በመረጥከው መንገድ ልጆችህ አለአባት ሲያድጉ ሌላው በሞቀ ጎጆ ልጆቹን ምንም እንዳልተፈጠረ እያሳደገ እኮ ነው! እንደው ለእኔ እንኳን ብለህ ባይሆን ለልጆችህ ስትል የሚሉህን ሁሉ እሺ ብለህ ከዚህ ብትወጣ ምን አለ? ልጆቻችንን አርፈን ብናሳድግስየምትል ሚስት ስለሌለን ነው ?
በእኔ እስር ምክንያት ባለቤቴ ልጆቼን ለማሳደግ ስራዋን አቁማ በሽታ ላይ ወደቀች፡፡ ልጆቼንም እነዳልንከባበብ ሆንኩ አግኝቻቸው ለማላውቃቸው ሰዎች ነጻነት ስል ከምንም አብልጬ የምወዳቸው ልጆቼ ጉሮሮ ላይ መቆም ምን ያህል ትክክለኛ ምርጫ ነው ?” የሚል ጭንቅላት የሚበጠብጥ አጣብቂኝ ስለሌለብን ነው ?
በዚህ እድሜዋ እናቴን መጦር ሲገባኝ ልጄ ታሰረ ብላ ጭንቀት ውስጥ እንድትገባ እና የአእምሮ እረፍት አንድታጣ ምክንያት ሆንኳት አንድ ልጅ ወልደህ ዓይኔን በዓይኔ አሳየኝ ልመናዋን እንኳን ሳላሳካላትየሚል ቁጭት ስለሌለን ነው ?ልጅ ሆኜ በማስፈልጋት ሰአት እናቴ ተገቢው ህክምና እንኳን ማግኘት አንድትችል ሳላግዝ አጣኋት፡፡ አሁን ደሞ ሽማግሌ አባቴ እንክብካቤ በሚፈልግበት ጊዜ ጭራሽ እስር ቤት ገብቼ እሱን አመላልሳለሁ እድሜዬን ሙሉ ሊያስተምረኝ ጥሪቱን ማፍሰሱ ሳያንስ አሁንም እዳው ሆኛለሁ የልጅነት ሃላፊነቴን የምወጣበት ጊዜ አገኝ ይሆን?” የሚል አስጨናቂ ፍርሃት ውስጣችንን ስለማይበላው ነው ?
የወጣትነት እድሜሽን አታስበዬ፣ አይምሰልሽ እድሜሽ እየገፋ ሲሄድ ይቆጭሻል፡፡ ልክ አንደ እኩዮችሽ ትዳር ይዘሽ ልጅ ወልደሽ የተረጋጋ ኑሮ አትኖሪም? ጊዜሽን አትቀልጂበት! የሚል መካሪ አጥተን ነው ?ትዳር ይዘን የተረጋጋ ቤተሰብ የምንመሰርትበት እቅድ ላይ ለምን እንቅፋት የሚሆን ስራ ትሰራለህ ? አላሳዝንህም? ምናልባት እኮ ከእስር ስትፈታ መውለድ የማልችልበት እድሜ ላይ ልሆን እችላለሁ? ደሞ ሕይወቴ አንተ ታስረህ እየደሄች እኮ ነው የሚል እጮኛ ስለሌለችን ነው ?
መንግስትን ማስገደድ የሚችል ጉልበት ያለን ስለመሰለን ነው ? ከእስር ወጥተን ራሳችንን የምናሳድርበት ሞያ ስለሌለን ነው ? ጀግና መባል ስለምንፈልግ ነው? እውቅና ዝና ፍለጋ ወይስ ልበ ደንዳናነት ነው?
ምንድነው እስር ቤት ያስቀመጠን ?"

ለሁሉም ጥያቄዎች መልሱ አይደለም ነው እንደማንኛውም ሰው ሁሉ ልንጦረው የምንፈልገው እናት ወይም አባት በእንክብካቤ ልናሳድጋቸው የምንፈልጋቸው ልጆች መስዋዕትነት የተከፈለበት የፍቅር ግንኙነት ወይም ትዳር አለን፡፡ 
ህይወታችንን ሁሉ እነሱን ለማስደሰት ስንደክም የማይሰለችን እና የማይበዛባቸው ሰዎች በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ አሉ ፡፡ዝና ጀግና መባል ሁሉ ያለእነሱ ትርጉም የሚያጣበትና እስር ቤት ሆነን የምንወዳቸው እና የመኖራችን ትርጉም የሆኑትን ሰዎች ደስታቸውና ምኞታቸውን ነጥቀናቸዋል፡፡ 
የሚመኙትን እና የምንመኝላቸውን ህይወት እንዳይኖሩ እንቅፋት ሆነናል፡፡ የሚወዱትን ሰው ደስታ እንዳያገኝ እንቅፋት ከመሆን ሕመም ጋር የታሰርነው በመታሰራችን የምናጣው ነገር ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፡፡ 

ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ የኢትዮጵያ የፓለቲካ እስረኞች የምር ድምጾች ናቸው ፡፡ ( ለዚህ ጽሁፍ ሲባልም የተፈጠረ ወይም የተጨመረ ነገር የለም
እነዚህ ጩኸቶች መልስ የሚያገኙት መቼ ይሆን
ይሄ ጥያቄ አንድ የወዳጄ የጦማሪ በፍቃዱ ጽሁፍን ያስታውሰኛል "80 ሚሊዮን እስክንደርስ እንታገላለን! "

No comments:

Post a Comment