Saturday, March 30, 2013

#Ethiopia: ሁለት ማስታወሻዎች ለኢሕአዴግ


-------------------
በዋሲሁን አወቀ
-------------------

አንድ፡- ኢሕአዴግ ሆይ የምትናገረውን የምትተገብር ድርጅት ያድርግህ!!!

የፌደራሊዝም ነገር

እነሆ ከጥቂት ወራት በኋላ 22ኛ የልደት በዓሉን የሚያከብረው ኢሕአዴግ በአባላቱ እና በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን አስተያየትና ትችት ለመቀበል አሻፈረኝ እንዳለ የአንድ ወጣት ዕድሜ ሞላው፡፡ ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዚያትና አጋጣሚዎች የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እንዳስከበረ፣ በብሄራዊ ድርጅቶች መካከል ፍትሐዊ የሥልጣን ክፍፍል እንዳደረገ እና በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ የዕድገት ደረጃ እንዳለ ሲናገር ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በተግባር ያለውና በኢሕአዴግ እየተነገረ ያለው አልገናኝ ብሎ ያስቸገረኝ እኔን ብቻ አይመስለኝም፡፡የብሔር ብሔረሰቦች መብት ተከበረ ሲባል ሁሉም ብሔር በሔረሰቦችና ሕዝቦች በዕኩልነትና በመፈቃቀድ በጋራ የሚኖሩበት ሁኔታ ሲመቻች እና በሀገሪቱ ባለው አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ እኩል ተሳታፊ መሆን ሲችሉ ነው፡፡ ይህ ግን ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ ሲተገበር አላየሁም፡፡

አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት አንድን መንግሥት እንደመንግሥት ፀንቶ እንዲቆይ ከሚያስችሉት ነገሮች መካከል የመንግስት ጠንካራ መዋቅር ዋነኛው ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ውጭ ጉዳይ ፣የጠቅላይ ሚኒስቴር/ፕሬዚዳንት ስልጣን (እንደየሀገራቱ የመንግሥት አወቃቀር ይወሰናል) ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡በኢሕአዴግ የስልጣን ዘመን እነዚህ አራቱ ክፍሎች ከአንድ ብሔር በተገኙ ግለሰቦች እጅ ለበርካታ ጊዜ የቆዩና አሁንም የቀጠሉ ናቸው፡፡ መከላከያን ለምሳሌ ብንወስድ እንኩዋን ከጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ያሉ አመራሮች በአብዛኛው ከአንድ ብሔር የተገኙ መሆናቸው አስፍኜዋለሁ ያለውን ዕኩልነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ የደኅንነት ቢሮው እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መ/ቤቶችም ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ መታማታቸው አልቀረም፡፡እንደውም ሁለቱን ቦታዎች ከእነሱ ውጭ ለመያዝ የሚያስብ ውጉዝ ከመአርዮስ የተባለ ይመስል እንደ አባት ርስት እየተፈራረቁ በውርስ መልክ ይዘዋቸዋል፡፡ ጠ/ሚኒስቴርነቱም ቢሆን በሰው እንጅ በአሠራር እና በአስተሳሰብ ነጻነቱን አላወጀም ብየ አምናለሁ፡፡

Thursday, March 28, 2013

እስር ቤቶቻችን በሕገ-መንግሥት ወይንስ በ‹‹ሕገ-አራዊት››?

እስርቤቶቻችንና ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች

---------------------
በጌታቸው ሺፈራው
---------------------
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን እንዲጸድቅ በበላይነት የመሩት አቶ መለስና አቶ ሌንጮ ለታ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ይህ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ባልሆኑት የተገንጣይ መሪዎች ጠንሳሽነት የጸደቀው ሕገ መንግሥት ለአገር ሉኣላዊነት፣ አንድነትና ታሪክ ክብር የሌለው ቢሆንም ዓለማቀፋዊ የሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አጠቃልሏል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለእርዳታ ማሰባሰቢያ የተቀመጡ እንጂ ወደመሬት ወርደው ተግባራዊ መሆና ባለመቻላቸው የይስሙላህ ሕግ ሆኗል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ የገዥዎች ጊዜያዊ ሥልጣን ጥቅም ለማስጠበቅ በየጊዜው ትርጉሙ የሚቀያየረው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ‹‹መርሕ›› ሕዝብ ላይ የተጫነ ገዥ ሕግ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይህን ስርዓት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ‹‹ሕገ አራዊት›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ በዚህ ስርዓት ሕዝብ በሕግ ስም እንጂ በሕግ የሚዳኝበት አጋጣሚ አይታይም፡፡ ብዙዎቹ በዚህ ስርዓት ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብም የታሰረ፣ ታስሮ የተፈታና ለወደፊት የሚታሰር እያሉ በቀልድ መልክ በሦስት የእስራት ምድብ ያስቀምጡታል፡፡ እንደ እኔ ሌላ አራተኛ ምድብም ሊካተት ይገባዋል፡፡ ይኸኛው እንደ ሦስቱ ምድቦች የአካል ጉዳትና ሰብኣዊ መብት ጥሰት የማይደርስበት ሕገመንግሥቱን አጽድቆ ራሱ የሚጥሰው አሳሪው ክፍል ነው፡፡ ይህ አሳሪው የኅብረተሰብ ክፍል በአካል ያልታሰረና ስርዓቱ እስካለ ድረስ በአካል ሊታሰርበት የሚችለው አጋጣሚ ጠባብ ቢሆንም የአዕምሮ እስረኛ ነው፡፡

ኢሕአዴግ እየዘመረለት የሚገኘው አቶ መለስና በእኩል ደረጃ የሚያወግዘው ‹‹አሸባሪው›› አቶ ሌንጮ ያጸደቁት ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች ምቹ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው በርካታ አንቀጾችን አስቀምጧል፡፡ ለአብነት ያህል አንቀጽ 19 (2) የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) ‹‹የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይንም ማንኛውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡›› ቢልም በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ የፕሮፖጋንዳ ፊልሞች ላይ ‹‹እማኝነታቸውን›› የሰጡ ታሳሪዎች የሚሰጡት ቃል በኃይል የተደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

Monday, March 25, 2013

#Ethiopia: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የመደራደር አቅማቸው (ክፍል 1)



በዳዊት ተ. ዓለሙ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የመደራደር አቅም (Bargaining power) ለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ስርአት ግንባታም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ላይ ተመስርቶ ለሚደረጉ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ስኬታማነት ወሳኝ ነው:: ሁሉን የፖለቲካ ቡድኖች ያማከለ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ምስረታም ሆነ የተቋማቱ ዘላቂነት በዋናነት የሚወሰነው የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚኖራቸው የመደራደር አቅም ልክ ነው:: ሚዛናዊ ያልሆነ የመደራደር አቅም ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሀካል በሚደረግ ስምምነት የሚፈጠሩ ተቋማትና ስርዓቶች በአመዛኙ ሊያስጠብቁ የሚችሉት ይበልጥ ጠንካራ የመደራደር አቅም ያለውን የፖለቲካ ኃይል ፍላጎቶች ነው:: ይበልጥ የዴሞክራሲ ስርአት ሰፍኖባቸዋል በሚባሉ ሀገራት ውስጥ በትንሹ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑና የተቀራረበ የመገዳደር አቅም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገኙባቸው ናቸው:: የተቀራረበ የመገዳደር አቅም ባላቸው ፓርቲዎች (መሪዎች) ድርድር የሚመሰረቱ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በአብዛኛው የሁሉንም ፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎቶች የማንጸባረቅ እዳላቸው የሰፋ ነው:: ለምሳሌ ያህልም ሮበርት ፑትናም Making Democracy Work ብሎ በሰየመው የምርምር ስራው ለ20 አመታት የኢጣሊያንን ፖለቲካ በቅርብ ከተከታተለ በኋላ ይህንን እውነታ በሰፊው አመልክቷል:: ስለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተቀራረበ የመደራደር አቅም ለሰላማዊ ፖለቲካና ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ወሳኝ ነው::

በሀገራችን የፖለቲካ ቡድኖች (ፓርቲዎች) የመደራደር አቅማቸው የማይመጣጠን በመሆኑ የመገዳደር ፖለቲካ ባህላችን በአፈሙዝ የበላይነት የሚደመደምበት እንዲሆን አድረጎታል:: በዚህም የተነሳ በየወቅቱ ሲገነቡ የነበሩት ተቋማት በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን ጥቅምና ህልውና የሚያስጠብቅ ባህሪና ቁመና የተላበሱ ሆነዋል:: የፖለቲካ ፓርቲ እሳቤና ተሞክሮ የሀገራችን የፖለቲካ ባህል ከተዋወቀበት ጊዜ አንስቶ የተመሰረቱ ፓለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም ሊያስብል በሚችል መልኩ የመደራደር አቅማቸው በጉልበት ላይ ወይም በተወሰ ጉዳዮች ላይ ብቻ የተነጠለጠለ ነው:: ይህም በመሆኑ በሀገራችን ደካማ ወይም ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የራቀው ፖለቲካዊ ባህል እንዲሰራፋ ሆኗል::

የመደራደር  አቅም ሲባል

Tuesday, March 19, 2013

#Ethiopia: የቀይ ለባሾቹ ውሎና አዳር


በበፍቃዱ ኃይሉ

ወጣቷ ዓለምን የቀን አጋጣሚ ስድስት ኪሎ አካባቢ፣ በዕለተ እሁድ (መጋቢት 8/2005) አንቀዥቅዦ አመጣት፡፡ በዕለቱ የለበሰችው የአዘቦት ቀይ ቲ-ሸርት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ለመዋል ምክንያት ይሆነኛል ብላ አልተገመተችም ነበር፡፡ በሰዓቱ የባለራዕይ ወጣቶች ማኅበር እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የኢትዮጵያውያን ጠላት የነበረው የፋሺስት ጣሊያን ጄኔራል ግራዚያኒን ኃውልት (በጣሊያን አገር፣ የትውልድ መንደሩ አካባቢ) መቆም በመቃወም የሰልፍ ጉዞ ከስድስት ኪሎ (የካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ኀውልት) እስከ ጣሊያን ኤምባሲ ድረስ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነበር፡፡ የሰልፉ ተሳታፊዎች ከጀርባው ላይ ‹‹ለግራዚያኒ ኀውልት ማሠራት አባቶቻችን የከፈሉትን መስዋዕትነት ማራከስ ነው›› የሚል ጽሑፍ የታተመበት ቀይ ቲ-ሸርት ለብሰው ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ካድሬዎች ደግሞ ‹‹ይቺ ባቄላ…›› በሚል ምክንያት ነው መሰለኝ ‹‹የተቃውሞ ሰልፍ…›› የሚባለውን ነገር ለማስቆም ራሱ ግብግብ ፈጥሮ፣ ራሱ ቀይ ለባሾቹን ማፈስ ሲጀምር ዓለምንም አብሮ አፍሶ አጋዛት፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት ለሥራ ጉዳይ ጓዙን ጠቅልሎ ወደአፋር ለመጓዝ እየጠበቁት ያሉ ባልደረቦቹን ለማግኘት በታክሲ ውስጥ ይጓዝ የነበረ አንድ ሰው ከስድስት ኪሎ ተነስቶ አምስት ኪሎ እስኪደርስ የተመለከተውን ሁካታ ዓይቶ ላለማለፍ ከታክሲ ይወርዳል፡፡ ፖሊሶች ከሰልፈኞቹ ውስጥ አሳደው የያዙትን እያፈሱ መኪና ውስጥ ሲያጉሩ፣ ከፖሊሶች ዕይታ እየተሰወረ በሞባይሉ ፎቶ ለማንሳት ሲሞክር፣ አንድም የረባ ፎቶ ሳያነሳ በሦስተኛው ፎቶ ላይ ከፖሊሶች ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጠመ፡፡ እሱም ተይዞ ተከተላቸው፡፡ ይህ ድንገተኛ እስረኛ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ሆነ፡፡

የታፈሱት ሰልፈኞች ሁሉ የታጎሩት በአራዳ ፖሊስ መምሪያ ጊቢ ውስጥ ነበር፡፡ ጊቢው ውስጥ እንደደረስኩ ከፊት ለፊቴ ደረጃው ላይ የተኮለኮሉትን ሰልፈኞች ተመለከትኩ፡፡ ወጣቶቹ ታፍሰው የገቡ ሳይሆን ወደው የተሰበሰቡ ይመስሉ ነበር፡፡ እንዲያውም በገባሁ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ጮክ ብለው ይዘፍኑ ጀመር፡-

‹‹… ተከብረሽ የኖርሽው ባባቶቻችን ደም፣ ባባቶቻችን ደም
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም…››

በዚህ ጊዜ ከፖሊሶቹ አንዱ አብሮ ሲዘምር ይታይ ነበር፡፡ ፖሊሶቹ የተሻለ ትሁቶች ቢሆኑም፣ ሲቪል ለባሾቹ ግን ማመናጨቅ እና ማዋከብ ዋነኛ ሥራቸው ነበር፡፡ እኔን በመኪና ይዘውኝ ከመጡት ውስጥ አንዱ ‹‹ዴሞክራሲ በዛ…›› የሚለውን ቃል እየደጋገመ በቁጭት ይናገራል፡፡ ብዙዎቹ የመምሪያው ፖሊሶች ከየት እንደመጣ የማያውቁት ኮማንደር ግን የተቆጨው በመዘግየቱ ነው፤ ‹‹ይሄን ያክል እስኪሰባሰቡ መቆየት አልነበረብንም›› አለ - እኔው ጎን ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ፡፡ በሬዲዮናቸው ሲለዋወጡ ከነበረው ውስጥም ‹‹ሱማሌ ተራ የተጎዳውን ሰውዬ የት ወሰዳችሁት?... ተክለሃይማኖት ሆስፒታል?...›› ይባባሉ ነበር፡፡ በዚሁ ጉዳይ ይሁን አይሁን ግን ‹‹መረጃም (ማስረጃም)›› አልነበረኝም፡፡

ጊቢው ውስጥ ከሌሎቹ እንዳልቀላቀልና ብቻዬን እንድቆይ አድርገውኛል፡፡ ባንድ በኩል ስልኬ ላይ ያሉትን ፎቶዎች አጥፍተው ይፈቱኛል፣ ጉዞዬም ይቀጥላል በሚል ደስ ብሎኛል፡፡ በሌላ በኩል በዓይን የማውቃቸውን እነዚያን ልጆች ቀረብ ብዬ አለማነጋገሬ ቆጭቶኛል፡፡ በዚህ መሐል ግን ሁሉም እየሄዱ ቃል ሲሰጡ ቆዩ (ቃል ሲባል ቃል እንዳይመስላችሁ፤ ከስም አንስቶ የኔ የምትሉትን ነገር በሙሉ ይጠይቋችኋል)፤ ከዚያም የኔም ተራ ደረሰና ቃል ሰጥቼ ሳበቃ እኔም በቀላሉ እንደማልሰናበት ሲያረዱኝ የጓዝ ኮተቴን ሁሉ አስመዝግቤ እዚያው ተጠቃለልኩ፡፡

ከዚያም ቃል የመስጠቱ ሥነ ስርዓት ቀጠለ፤ የመጣው ሁሉ በራሱ መንገድ ያንኑ ጥያቄ መልሶ፣ መላልሶ እያንዳንዱን ታሳሪ (ተጠርጣሪ ልበል ይሆን?) ይጠይቃል፤ እያንዳንዱም ተጠርጣሪ ይመልሳል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹን መርማሪዎች የብስጭት መንስኤ የሚሆን ነገር ባለራዕዮቹ ወጣቶች ሳይናገሩ አይወጡም ነበር፡፡ ብሔር ሲባሉ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ይላሉ፡፡ ይህንን የሚሉት ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹አገር›› መሆኑን እያጣቀሱ ነው፡፡ ታዲያ ይህ አባባል ለመርማሪዎቹ የሚያበሳጭ ድፍረት ነበር፡፡

ፖሊሶቹ የሆነችውን ሁሉ እየደወሉ፣ ለአለቆቻቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ መሐል ከሰልፈኞቹ አንዱ ለብሶት የነበረው ባንዲራ ላይ በእስክርቢቶ የጻፈውን ደብዳቤ ከስልኩ ወዲያ ላለ ሰው በንባብ ሲያጽፉት ሰምቻለሁ፡፡ ጽሑፉ ባብዛኛው መንፈሳዊ ነው ቢባል ይቀላል፡፡ ‹‹ለእመቤታችን በአስራትነት የተሰጠችው አገራችን ኢትዮጵያ…›› ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡

ምርመራው/ጥያቄው ቀጥሏል፤ ከጠያቂዎቹ መካከል የደኅንነት እና የኢንሳ ሰዎችም ነበሩበት፡፡ ከጥያቄዎቻቸውም ውስጥ የኢሜይል አድራሻ እና የይለፍ ቃል፣ የፌስቡክ አድራሻ እና የይለፍ ቃልም ይጠይቁ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ታሳሪ (ተጠርጣሪ አልልም) ስሙን በቪድዮ ካሜራ ፊት እንዲናገር ይገደድ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህንኛው መጀመሪያ ላይ እያንዳንዱ ሰው ከተነሳው ፎቶ በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የጅምላ እስር ውስጥ ካስተዋልኳቸው ጉዳዮች ውስጥ የሴቶቻችንን ጀግንነት ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ እኔ ያለምንም ማንገራገር ምስሌን አስቀርጬ ወደቃለመጠይቁ ሳልፍ የሰማያዊ ፓርቲዋ አመራር አባል ሐና ዋለልኝ ‹‹አልቀረጽም፣ አሻፈረኝ›› ብላ ስትሟገት ድምፅዋ ይሰማኝ ነበር፡፡

ሲመሽ ይፈቱን ይሆን? እዚሁ ያሳድሩን ይሆን? ሌላ ቦታ ይወስዱን ይሆን? ምን ብለው ይከሱን ይሆን? እየተባባልን የተሰባሰብንባት አንዲት በረንዳ መሳይ ክፍል ውስጥ፣ ኢቴቪ በቀጥታ የሚያስተላልፋቸውን የአዳማ እና የመቐለ የኦሕዴድ እና የሕወሓት ስብሰባዎች መኮምኮም ጀመርን፡፡ አሳሪዎቻችንም በስልክ አለቆቻቸውን እያነጋገሩ ሽር ጉዳቸውን አጧጡፈውታል፡፡ ኢቴቪም ብቻውን በዓሉን ማክበር አልቻለም፡፡ መብራቱ ብልጭ ድርግም አበዛ፡፡ ብልጭ ድርግም አልኩ እንጂ ያበዛውስ ድርግም ማለት ነው፤ አልፎ፣ አልፎ ግን ላፍታ ብልጭ እያለ ነበር፡፡ በጨለማው ውስጥ ራታችንን በጨለማ ተቋደስን፡፡ ሁላችንም ምሳ ያልበላን ቢሆንም አንዳንዶች ግን ቁርሳቸውንም አልበሉም፡፡

የመታሰራችን ዜና በማኅበራዊ አውታሮች በመጠኑ ቢስተገባም የብዙዎቻችን ቤተሰቦች ግን አልሰሙም፤ ደውሎ የማሳወቅ ዕድሉም አልተሰጠንም፡፡ እዚያው ጨለማ ውስጥ ከቆየን በኋላ ወደ 3፡00 ሰዓት ገደማ ወደ ጃንሜዳ አካባቢ የሚገኝ ማረሚያ (እስር ቤት) በሁለት ዙር ተወሰድን ከ30 በላይ እስረኞች አንድ ላስቲክ ብቻ ወለሉ ላይ የተነጠፈበት ክፍል ውስጥ ብንታጎርም በእርስ በርሳችን ጫወታ ተጠምደን ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ እኛ ወደዚህ እስር ቤት ስንዛወር ቀይ ለባሽዋ ዓለም ተለቅቃ ወደቤቷ ሄዳለች፡፡) የሄድንበት በሰልፉ ዋዜማ ሲቀሰቅሱ ከታሰሩ ሌሎች ጋር ተቀላቅለናል፡፡ የጅምላ እስሩ ጉዳይ በዋዜማው እንደተጀመረ ያወቅኩትም ያኔ ነው፡፡ ቀድመው ከታሰሩት ውስጥ ሁለቱ ክፉኛ ቡጢ እና ካልቾ ቀምሰው እንደሆነ ለማወቅ እስኪናገሩ መጠበቅ አያስፈልገንም ነበር፤ የአንደኛው ጃኬት የደረቀ ደም ከፊትለፊት ይታይበታል፡፡

ለአምስት ሰዓት ዐሥራ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን እንደገና እንድንንቀሳቀስ ተነገረን፡፡ ከኛ ቀደም ብለው ሴቶቹም ወደቀጨኔ (ችሎት መድኃኔዓለም ኮንዴሚኒዬም አጠገበ ያለ) ወረዳ 9 ማረሚያ ቤት እንደተወሰዱ እና ከኛም ውስጥ 12ቶቻችን መከተል እንዳለብን ተነገረን፡፡ እዚያ እንደደረስን ግን ምነው እዚያው በቀረን የሚያስብል ትዕይንት ገጠመን፡፡ እያንዳንዱ ክፍል እላይ በላይ ተደራርበው በተኙ እስረኞች ተጨናንቋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጫማ ማስቀመጫ ቦታ እንኳን በክፍሉ ውስጥ ስለሌለ ጫማዎቻችንን ውጪ እያስቀመጥን እንድንገባ ተገደድን፡፡ ሦስቱ (አራት ሜትር በአራት ሜትር የሚገመቱ) ክፍሎች ውስጥ አንዱ 37፣ አንዱ 34 እና ሌላኛው ውስጥ 30 እስረኞችን ይዟል፡፡

እንዳጋጣሚ 30 ሰዎች የያዘው ውስጥ ነበር እኔ የደረሰኝ፡፡ የኛ ክፍል ይሻላል ተብሎ ዶ/ር ያዕቆብንም አመጧቸው፡፡ ጉዳዩ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ እኛስ ባልደከመ ጉልበታችን እንችለዋለን፤ ለርሳቸው ግን በጣም ፈታኝ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው፡፡ ክፍሉ በጣም ጥቅጥቅ ብሎ ከመሞላቱ የተነሳ ለኛ ቦታ ለማግኘት የቤቱ ካቦ ተነስቶ እያንዳንዱን እስረኛ እየቀሰቀሰ ማጠጋጋት ነበረበት፡፡ በቦታ ጥበት ምክንያት ደረቁ ወለል ላይ በአንድ ጎናችን እንድንተኛ ከመገደዳችን የተነሳ እኔ ይህን ጽሑፍ እስከምጽፍበት ሰዓት ድረስ ቁርቋሬው የፈጠረው ሕመም ጎኔን አያስነካኝም፡፡ ካቦው አጠጋግቶልን ሲጨርስ ሁላችንንም የገቢ ገንዘብ ተቀበለን እና ተኛን፡፡ እዚያ ክፍል ውስጥ መተኛት ማለት፣ መተኛት ማለት አይደለም፡፡ የክፍሉ መታፈን እና አስቀያሚ ጠረን፣ ሙቀት፣ በዚያ ላይ እየተቀባበሉ የሚያጨሱት ሲጃራ ጢስ፣ ከዚያ እና ከዚህ የሚተኮስ የፈስ ሽታ… ብቻ የአበሳ ናሙና ነበር፡፡ ሌሊቱን ሲዘንብ ማደሩ ግን በከፊልም ቢሆን የክፍሉን አየር አቀዝቅዞታል፤ ችግሩ ዝናቡ ውጪ ያስቀመጥነው ጫማ ውስጥ ውኃ መሙላቱ ብቻ ነበር፡፡

እንደምንም ነጋልንና ወደፍርድ ቤት እንደምንሄድ ተነግሮን ጥንድ ጥንድ እየተደረግ በካቴና ተቆላለፍን፡፡ ከመሐከላችን አንዱ የማኅበሩ አባል፣ ፀጉሩን አጎፍሮ ስለነበር (ለፍርድ ቤቱ ውበት አይመጥንም ብለው ይሆናል) ይቆረጥ አሉና መቀስ አንስተው ይከመክሙት ጀመር፡፡ ፀጉሩን ቆርጠው ሲጨርሱ አሰለፉንና ካቴናችንን ፈቱት፡፡ ‹‹ፍርድ ቤት መወሰዳችሁ ቀርቷል፣ ምናልባት ፖሊስ ጉዳዩን ይፈታዋል›› ተባልንና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወደጃንሜዳ ማረሚያ ቤት መልሰው ወሰዱን፡፡ እዚያ ስንደርስ ለፖሊስ ዋስ እያቀረብን እንድንፈታ ተፈቀደልን፡፡ ቀድሞውንም የታሰርነው ያለወንጀል በመሆኑ አስገራሚ ውለታ አልነበረም፡፡

የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የሚያስፈልገው ቅድመ ሁኔታ ለመስተዳድሩ ማሳወቅ ሲሆን፣ መስተዳድሩ ደግሞ በ24 ሰዓት ውስጥ ‹‹አይሆንም›› የሚል ደብዳቤ ካልጻፈ እንደተፈቀደ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ሰልፍ ማድረጉ ሕጋዊ ስህተት የለበትም፣ ጉዳዩ ባንድ ጀምበር የተወለደ ሳይሆን ጋዜጦች ዜና የሰሩለት፣ ቁጥቦቹ ሬድዮዎች ሳይቀሩ ያወሩለት ጉዳይ ስለሆነ ወንጀል ነው ፍርድ ቤት ሊያቀርቡት አይችሉም/አይገባቸውምም፡፡ ነገር ግን ‹‹…ካፈርኩ አይመልሰኝ…›› ይመስላል በዋስትና እንድንፈታ ፈቅደው ያገቱብንን ንብረቶቻችንን እየመለሱ መጋቢት 9/2005 እኩለ ቀን ላይ አሰናበቱን፡፡

Friday, March 15, 2013

#Ethiopia: የዘር ፖለቲካ አዳላጭነት (ለበፍቃዱ ኃይሉ ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ)


በዳዊት ተሾመ

ኢትዮጵያ፣ ትግራይ እና ህውሓት ምንና ምን ናቸው? በሚል ርዕስ በበፍቃዱ ኃይሉ የቀረበው ጹሑፍ በአሁኑ ወቅት በዋናነት የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ  የሚያጠነጥነበትን ነገር ግን በአብዛኛው ለግልጽ ውይይትና ክርክር፣ ለመድረክ ያልበቃ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ነው:: ለመድረክ ያለመብቃቱ ምክንያት በአብዛኛው ግልጽ ውይይት ያላደበርን በመሆናችንና ከብሔር ፖለቲካ ስስነት ጋር የተያያዘ ይመስለኛል:: በተጨማሪም ብዙዎቹ የሀገራችን ምሁራን በጉዳዩ ላይ የተለያዩ መጽሐፍቶችና ጹሑፎችን ቢጽፉም፤ የጻፉበት ቋንቋ በአብዛኛው በእንግሊዘኛ ስለሆነና የጻፉትም ለውጭ ታዳሚዎቻቸው ስለሆነ የጉዳዩ ባለቤት ባዳ እንዲሆን አድርጎታል:: ይህንን ዝግ ጉዳይ ጸሐፊው ለመስበር መሞከሩ በርታ የሚያስብል ነው:: ጽሑፉ ብዙ የምስማማባቸውን ሐሳቦች ያዘለ ነው:: ሆኖም ግን፣ በዚህ ጽሑፌ ሊታዩ ይገባቸዋል ብዬ ያሰብኳቸውን፣ ጸሐፊው በግልጽ ያላስቀመጣቸውንና በተወሰነ መልኩም አመክኖያዊ ግድፈቶችን ለመጠቆም ያህል ነው::

(1).
በሳይንሳዊ ምርምር ምልዕ-እውነት (100% truth) የሚባል ነገር የለም:: ምርምር በራሱ ማስረጃዎች ላይ የተደገፈና በተወሰነ ንድፈ-ሐሳባዊ መሠረት ተመስርቶ  በመከራከር፣ በመቃወም፣ እንዲሁም አዳዲስ ዕሳቤዎችንና ዕይታዎችን በማፍለቅ ወደ እውነት በተቻለ መጠን የመጠጋት ሒደት ነው:: ስለዚህም እውነት አንጻራዊነትን (relativity) የሚላበስ እንጂ ሁለንተናዊ (absolute) አይደለም:: ስለሆነም፣ ለአንድ ሰው ውይም ቡድን በአብዛኛው እውነት የሆነው ነገር ለሌላው ሰው ውይም ግሩፕ  እውነት ሊሆን እንደማይችል ታሳቢ መደረግ ያለበት ጉዳይ ነው:: በአንድ የተወሰነ ሐሳብ ውይም ጉዳይ ላይ የተለያዩ ዕይታዎችን (school of thoughts) የምናገኘው ለዚህ ነው::

Tuesday, March 12, 2013

#Ethiopia፣ ትግራይ እና ሕወሓት ምንና ምን ናቸው?


በበፍቃዱ ኃይሉ

“An event has happened, upon which it is difficult to speak, and impossible to be silent.’ ~ Edmund Burke.

ሴቶች!

ሴቶች ፀጉራቸውን ያሳድጋሉ፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር በስህተት የተደነቀረ አይደለም፤ በምሳሌነት የቀረበ ነው፡፡ 1ኛ. ፀጉራቸውን የማያሳድጉ ሴቶች አሉ፤ 2ኛ. ፀጉራቸውን የሚያሳድጉ ወንዶችም አሉ፡፡ ቢሆንም ግን ዓረፍተ ነገሩ ውሸት/ስህተት ነው ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም የተለዩት (exceptionals) አጠቃላዩን አይገልፁም፡፡ በዚህ ርዕስ ስር የምናወራው ፍፁም እውነት ስለሆነ ነገር አይደለም፤ በአብዛኛው እውነት ስለሆነ ነገር ነው፡፡

ሕወሓት!

የትግራይ ተወላጆች ሕወሓት ይደግፋሉ፡፡ የዚህ ዓረፍተ ነገር እውነትነት ልክ ‹‹ሴቶች ፀጉራቸውን ያሳድጋሉ፡፡›› እንደሚለው ዓረፍተ ነገር ነው፡፡

በቁጥር ውዥንብር (illusion) ውስጥ ካልገባን በቀር (ኢሕአዴግ የደጋፊዎቼ ቁጥር እያለ የሚናገረው የ‹‹እውነተኛ›› ደጋፊዎቹ ቁጥር ነው ብለን ነባራዊውን እውነታ ማገናዘብ ካልተሳነን በቀር) የሕወሓት/ኢሕአዴግ ደጋፊዎች ቁጥር ከትግራይ ተወላጆች ቁጥር ጋር እኩል ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ትክክልም/ስህተትም አይደለም/ነውም፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብም ሆነ ማንኛውም ሰው የፈለገውን በሙሉ ወይም በጎዶሎ ድምፅ መደገፍ ይችላል፡፡ ስህተቱ ግን ምክንያቱ ላይ ነው - ወደእዚህ እንመለስበታለን፡፡

ሌላ እውነት፤ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ደጋፊዎች ቁጥር ከትግራይ ተወላጆች ቁጥርጋ እኩል ከሆነ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሓትን ወይ ይቃወማል አሊያም አይደግፍም ማለት ነው፡፡ ይኼም ትክክልም ስህተትም አይደለም/ነውም፡፡

በመጀመሪያ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምን ሕወሓትን አይደግፉም ወይም ይቃወማሉ? (ለምን ‹ሕወሓት› አልኩኝ? በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምናወራው ወረቀት ላይ የሰፈረውን ማደናገሪያ ሳይሆን በተግባር ላይ ያለውን እውነታ ነው፤ ስለዚህ የመንግሥት ስልጣን ያለው በኢሕአዴግ እጅ ሳይሆን በሕወሓት እጅ መሆኑን ማስታወስ ይበልጥ ያግባባናል፡፡) ለጥያቄው መልስ ስንሰጥ፡-

Friday, March 8, 2013

#Ethiopia፡ ሴት የመሆን ጥቅሞችና መታደሎች

በሶሊያና ሽመልስ

ሴት መሆን መታደል ነው ብዬ ብጀምር  የሚስቅብኝ አይጠፋም! ሴት የመሆን ጉዳቶች ላይ ተደጋጋሚ ነገር ሲነገር ሰምተናል፡፡ የቤት ውስጥ የሥራ ጫናው፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱ፣ የዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶቹ፣ ከወንድ ይልቅ ለባሕል እና ለማኅበረሰብ የመገዛት ኃላፊነት ላያችን ላይ መጫኑ፣ የሚታየው አካላዊ ጉዳት (አሲዱ፣ አስገድዶ መድፈሩ፣ ድብደባው…) የማይታየው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት (እኔ፣ አንቺ፣ እናቶቻችን ሁላችንም የምናልፍበት የአእምሮኣዊ ጭንቀት ሐሳብ እና ትግል) ሁሉም በተደጋጋሚ ተወርቶላቸዋል፡፡ የሴቶች ቀን ላይ ቆመን ሴት የመሆን ጥቅሞች እና ደስታዎች ላይ ለመጻፍ ብንነሳ ማን ይከለክለናል?

የሴቶች ቀን ሲነሳ ‹‹ሌላው የወንዶች ቀን ነው፤›› የሚል ተራ ክርክርን በዚሁ ነካ አድርጌ ልለፍ፡፡ ማርች 8 የሴቶች ቀን ሲሆን ሌሎቹ የሰዎች ቀናት ናቸው፡፡ የወንድም፣ የሴትም፣ የሕፃንም፣ የሽማግሌም፣ የነጋዴም፣ የወጣትም… - የሁሉም ሰዎች ነው፡፡ የአባቶች ቀን፣ የእናቶች ቀን፣ የበዓላት ቀን ነገር ሲነሳ ይህ ክርክር ትዝ የማይላቸው ሰዎች ለምን ‹‹የሴቶች ቀን›› ላይ ብቻ እንደሚበረቱ አላውቅም?!