Tuesday, April 28, 2015

ስቃይና መብት ጥሰት -አጥናፍ ብርሃኔ

አጥናፍ ብርሃኔ 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ
- ሳጅን ምንላድርግልህ
-ታደሰ ወይም ጥጋቡ ( የሽፋን ስም )
- ኢንስፔክተር አሰፋ
- ም/ሳጅን መኮንን
- ኢንስፔክተር ገብሩ
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 17 እስከ ሃምሌ 11 /2006 አም

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ በተለይ ቢሮ ቁጥር 5.፣ 32

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- ታደሰ የተባለው መርማሪ ፓሊስ ያለምንም ምክንያት ምርመራ ክፍል ውስጥ እያነቀኝ በተደጋጋሚ “እውነቱን የማትናገር ከሆነ ሽባ ነው የምናደርግህ ፣ እኛ ለግለሰብ መብት አንጨነቅም” በማለት በጥፊ ሲደበድበኝ ነበር

- ሳጅን ምን ላድርግልህ የተባለ መርማሪ “ጦማር ምን ማለት አንደሆነ ተናገር” ሲለኝ ጦማር ማለት መጻፍ ነው ብለውም ፡።፡።”ምህጻረ ቃል ነው እያንዳንዷ ምጻረ ቃል ምን ማለት አንደሆነች ካልተናገርክ አንላቀቅም” በማለት ከግርግዳ ጋር እያጋጨ ደብድቦኛል፣ ከግርግዳ ማጋጨት ብቻም ሳይሆን ረጅም ሰአት ከአቅሜ በላይ የሆነ የአካል አንቅስቃሴ እየሰራሁ የተመረመርኩ ሲሆን ምራቁን እየተፋብኝ አጸያፊ ስድብ ሲሰድበኝ ነበር፡፡

- ግንቦት ወር ላይ ሳጅን ምን ላድርግልህ የተባለው መርማሪ “ ኢህአዴግን ለምንድነው ተችታችሁ የምትጽፉት ?” “ከአገር ውጪ የምትሄዱት የመንግሰትን ስም ለማጥፋት ነው አንጂ የአባይ ግድብ ቦንድ ለመግዛት አይደለም” በማለት እጄን ወደላይ አድርጌ አንድመረመር አንዲሁም ጆሮዬን እየጎተተ በጥፌ ሲደበድበኝ ውሏል፡፡ ከዚህ ቤት ደንቁረህ ነው የምትወጣው በማለትም ያስፈራራኝ ነበር፡፡ እየተፋብኝ አጸያፊ ስድብ እየተሰደብኩ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ተፈጽሞብኛል፡፡

- በሰኔ ወር ኢንስፔክተር አሰፋ የሚባለው መርማሪ ሌሊት 6 ሰአት አካባቢ ጠርቶኝ አላማችሁን ካልተናገርክ ጭለማ ቤት ነው የምትገባው በማለት ከማስፈራራቱም በላይ ሌሎች እስረኞች ሲደበደቡ እና ሲጮሁ ሲያለቅሱ በማሰማት እነደነሱ አንዳትሆን በማለት ዛቻ ተፈጽሞብኛል።

- ሰኔ ወር ላይ ኢንስፔክተር ገብሩ የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ በመግባት ወረቀት ጽፈሃል የሚል በውል በማላውቀው ምክንያት ከሌሎች እስረኞች ለይቶ በተኛሁበት በተደጋጋሚ ከባድ የእርግጫ ደብደባ ፈጽሞብኛል። ሲደበድበኝም ህዝብ ልታጫርስ ነው እያለ ነበር፣ አስካሁንም የዛን ቀኑን ድብደባ ምክንያት ነው ያሉትን ነገር አላውቀውም፡፡

- በማእከላዊ ቆይታዬ 4በ4 በሆነች ክፍል ውስጥ በቀን ሁለቴ ብቻ ለ15 ደቂቃ ወደውጪ በመውጣት ከአስር ሰው ጋር ተቆልፎብኝ ታሬያለሁ ፡፡ የመጸዳዳት እድልም ቀኑን ሙሉ አልነበረኝም ፡፡ በየቀኑ ከባድ የአካል አንቅስቃሴ መስራት የምርመራው አካል ነበር፡፡

- በሃምሌ ወር ከምሽቱ 2.30 አካባቢ ሳጅን ምንላድርግልህ ፣ ም/ሳጅን መኮንን እና ሌላ የማላውቀው መርማሪ በመሆን ጭንቅላቴን በሃይል ከግንብ ጋር በማጋጨት እና የኮምፒውተር ኬብል በማሳየት አንደምገረፍ በመንገር ሳጅን ምንላድርግልህ የተባለው መርማሪ ፓሊስ የጻፈው የእምነት ቃል ላይ በግዳጅ አንድፈርም ተገድጃለሁ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው 

ስቃይና መብት ጥሰት - አስማማው ሐይለጊዬርጊስ

አስማማው ሐይለጊዬርጊስ 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ ስማቸው የማላውቃቸው ማንነታቸውን ለመናገር ፍቃደኛ ያልሆኑ አራት መርማሪዎች እና መርማሪ ጽጌ መርማሪ መኮንን አብተው

ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 17 እስከ ሃምሌ 11 /2006 አም 

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ላይ

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- ከአንድ ወር ከአስራም አምስት ቀን በላይ የተፈጥሮ ብርሃን የሌለው በጨለማ ክፍል ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ታስሬያለሁ

- የቀለም አብዮት ልታመጣ ነው የወጠንከው በሚል ስለቀለም አብዬት እቅድ ተደጋጋሚ ተጠይቄያለሁ፡፡

- ስታሰር ከመንገድ ላይ የታፈንኩ ሲሆን ምንም አይነት ጥያቄ አንድጠይቅ አልተፈቀደልኝም፡፡ የእስር ትእዛዝ አላሳዬኝም ፣ የእስር ትእዛዝ አሳዬኝ ብዬ ብጠይቅም መልስ አልተሰጠኝም፡፡

- ባለብኝ የወገብ ህመም የተነሳ ወንበር አንዲገባልኝ ብጠይቅም ለ65 ቀናት ከፍተኛ ህመም ስር ሆኜ ቆይቻለሁ ፡፡ አካላዊ ጤንነት የመጠበቅ መብቴ ተነፍጓል፡፡

- “የአንተ ነገር አልቆለታል ፡፡ነጻ ሰው ነኝ ማለት አትችልም ወንጀልህን ተናዘዝ” የሚል ረጅም ሰአት ማስፈራሪያ ደርሶብኛል

- የሙያ ባልደረቦቼን ውብሸትን ታዬን እና ሌሎች ታራሚዎችን መጠየቄን አንደወንወጀል ተቆጥሮ ለምን ጥሩ ታራሚዎችን አትጠይቀም በሚል ከፍተኛ ተሳልቆ ደርሶብኛል፡፡

- በር በሌለው መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም የተገደድን ሲሆን በቀን ለ10 ደቂቃ ብቻ ጸሃይ ብርሃን አገኝ ነበር ፡፡

- ስድብ መሳለቅ ያንተ ነገር ያለቀለት ጉዳይ ነው በማለት ከፍተኛ ስፓርት አንድሰራ እና የዞን9 አባል ነኝ ብዬ አንዳምን ከፍተኛ ማሰቃየት ደርሶብኛል ፡፡

- በካቴና ታስሬ እየተመረመርኩ ቢሆንም አንተ ጭራሽ ተመርማሪ አትመልስልም በሚል ተራ ምክንያት ማሰቃየት እና ጥፊ የተለመደ ነበር ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው  

ስቃይና መብት ጥሰት - ማህሌት ፋንታሁን

ማህሌት ፋንታሁን 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት እና የፌደራል ደህንነት መስሪያ ቤት አባላት መርማሪ ደስታ በዋናነት
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - በተያዝኩባቸው ቀናት በሙሉ (በተለይ ሚያዝያ 18 በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በሰፊው) 

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ቢሮ ላይ
ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት

- በጠበቃ እና በቤተሰብ የመጎብኘት መብቴ ተጥሷል፡፡ ከተጎበኘሁም 10ደቂቃ ለማይሞላ ጊዜ በፓሊስ ተከብቤ ነበር፡፡

- በተደጋጋሚ በምርመራ ወቅት አመጽ ለማነሳሳት እነደጸፍሽ እመኚ እየተባልኩ በጥፊ እና በካልቶ ተደብድቤያለሁ፡፡

- በምርመራ ወቅት ልብሴን አስወልቀው አንድቀመጥ በማድረግ አይኔ ተሸፍኖ በምሽት ምርመራ ተደርጎብኛል፡፡

- ሙሉ ልብሴን እንዳወልቅ ተገድጄ ራቄቴን በወንድ መርማሪዎች ፊት ስፓርት አንድሰራ እገደድ ነበር ፡፡ “ሴትነትሽ አንዲህ ከሚዋረድ አመጽ እንዳነሳሳሽ እመኚ ተብያሁ”

- በሌሊት ግርፋት የሚፈጸምበት ክፍል ውስጥ ገብቼ ጫማሽን አውልቂ ተብዬ ጫማዬን አውልቄ ከቆምኩ በኋላ ውስጥ እግርሽን ከምትገረፊ አመጽ ማነሳሳትሽን አምነሽ ፈርሚ ተብያለሁ፡፡

- ሰጠሁት የተባለው ቃል ሰዎች በሚቀጥለው ክፍል እየተደበደቡ የጩኀት ድምጻቸው እየተሰማ ፈርሚ ተብዬ የተባልኩት ቦታ ላይ ሳላነብ በፍርሃት ፈርሜያለሁ።

- በተለያዬ ምርመራ ወቅቶች "ለነጭ አገሪትዋን የሸጥሽ ሸርሙጣ ውሻ ባንዳ..." አንዲሁም ለመጸፍ የሚከብዱ አፀያፈ ስድቦች በየቀኑ እሰደብ ነበር ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

ስቃይና መብት ጥሰት - ኤዶም ካሳዬ

ኤዶም ካሳዬ
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት እና የፌደራል ደህንነት መስሪያ ቤት አባላት መርማሪ ደስታ በዋናነት

ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - በተያዝኩባቸው ቀናት በሙሉ በተለይ ሚያዝያ 18 ,20, 21, 22, 23
የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ቢሮ ላይ
ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት

-መርማሪዬ ደስታ በተደጋጋሚ በጥፊ ይመታኝ ነበረ ሲሆነ ከዚህ ቤት የፈለግነውን ልናደርግሽ እንችላለን በአካል አትወጪም እያለ አስፈራርቶኛል

-የዞን 9 አባል አይደለሁም በማለቴ ፌቴን አዙሬ ከባድ የአካል አንቅስቃሴ የሰራሁ ሲሆን በተጨማሪም አላማቸውን ተናገሪ ሲለኝ የተለየ አላማ እንዳላቸው አላውቅም በማለቴ ሳታውቂ አንዴት አብረሻቸው ትውያለሽ ሸርሙጣ ብሎ በተደጋጋሚ ሰድቦኛል፡። ሌሎቹ መርማሪዎች አብረው ተቀምጠው በስድቦቹ ይስቁ ነበር

-ሌላኛው ተከሳሽ አጥናፍ መደብደቡን ፍርድ ቤት በመናገሩ አንቺ ትሞክሪውና ዋጋሽን ታገኛለሽ እኛ ፍርድ ቤት አያዘንም የግለሰብ መብትም አያሳስበንም ብሎኛል

-ጥጋቡ የሚባለው መርማሪ ምርመራ መሃል ደንገት በሩን ከፍቶ ገብቶ በጥፊ መቶኝ ይወጣ ነበር ( ስለምናወራው ጉዳይም ሆነ ስለምርመራው ሳይሰማ) እምቢ ካለችህ ልብሷን አስወለወቀህ ግረፋት ብሎ እኔን የተለመደውን ስድብ ሰድቦኝ ሄዷል

-በምርመራ ወቅት የዞን አባል ነኝ ብለሽ እመኚ ተብዬ ልብሴን አውልቄ ሙሉ እርቃኔን አንድመረመር ተገድጃለሁ ፡። በጥፊ እመታ የነበረ ሲሆን በዚህ ቀን ምርመራው ምሽት ላይ ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6 ሰአት ቆይቷል

-በተለምዶው ከምመረመርበት ቢሮ ውጩ አንደኛ ፎቅ አዳራሽ ውስጥ ለምርመራ ተወስጄ ልብሴን እንዳወልቅ እና የተለያዬ ለመናገር የሚከብዱ ስፓርታዊ አንቅስቃሴዎችን እንድሰራ ተገድጃለሁ፡፡ እንዲህ ከምትዋረጂ አመጽ ልናስነሳ ነበር ብለሽ ለምን አታምኚም እያለ ይመታኝ ነበር ፡፡ በጥፊው ተደጋጋሚነት የተነሳ ታምሜ ክሊኒክ ተመላልሻለሁ::

-በጋዜጠኝነት ሞያየ የተሳተፍኩበትን ስልጠናዎች ስናገር አንቺ ለምን ተመረጥሽ የኢቲቪ ጋዜጠኞች ለምን አይሄዱም አንቺ ለፈረንጅ ስለምትሰልዬ ነው ብሎኛል፡፡ በተጨማሪም ዞን9 ላይ የሚወጡት ጽሁፎች አንድ ገጠር ያለ ሰው ቢያነበው ለአመጽ የሚያነሳሳው ልማቱን የሚያጣጥል ነው ብሎ በተደጋጋሚ በጥፊና በካልቾ ተመትቻለሁ፡፡

-በተጨማሪም በተፈቺ እስረኛ ወደውጪ መልእክት ልከሻል በሚል ሰበብ ሌሊት ተጠርጬ በዱላ ሲዛትብኝ አርፍዷል

-በእስሩ ወቅት ከማህሌት ፋንታሁን ጋር ለብቻችን ከሰው አንዳንገናኝ ተደርገን ቆይተናል፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው

ስቃይና መብት ጥሰት - ዘላለም ክብረት

ዘላለም ክብረት
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት እና የፌደራል ደህንነት መስሪያ ቤት አባላት መርማሪ ታደሰ ወይም ጥጋቡ ( ስሙ በትክክል የማላውቀው) በተለይ መርማሪ ምን ላድርግልህ መርማሪ ጽጌ መርማሪ አብዱልመጂድ
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - በተያዝኩባቸው ቀናት በሙሉ በተለይ ሚያዝያ 17፣ ሚያዝያ 22 ሚያዝያ 25 እና ግንቦት 9
የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ ቢሮ ላይ
ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- በታሰርኩነት ወቅት ህጋዊ የእስር እና የብርበራ ትእዛዝ አልነበረም፡፡ ህጋዊ ያልሆነ ፍተሻ ከ12 ሰአት በኋላ አታድርጉ ብልም የሚሰማኝ አላገኘሁም ፡። ፍተሻው በከፍተኛ ማስፈራሪያ የታጀበ ነበር፡፡ ፓሊስ ጣብያ እሄዳለሁ ብለህ እንዳታስብ ራስህን ለምትሄድበት ቦታ አዘጋጅ እያሉ ከፍተኛ ስነልቦና ጫና አድርሰውብኛል
- በመጀመሪያው ቀን ፍርድ ቤት ስንቀርብ ትምህርቴን አጠናቅቄ ላስረክበው ያዘጋጀሁትን የመመረቂያ ጽሁፍ ፓሊስ መያዙን እና ኮፒ አድርጌ እንዳስረክብ ይፈቀድልኝ ብዬ ስጠይቅ ፍርድ ቤቱም መብቱ ነው ብሎ ትእዛዝ ቢሰጥም ፓሊስ ትእዛዙን ተግባራዊ አንዲያደርግ ብጠይቅ የማዕላዊ ወንጀል ምርመራ ሃላፊ ኢንስፔክተር “ፍርድ ቤት እኛን አያዘንም“ ” የት ያለህ መሰለህ” ዳኛዋ ታስረክብልህ” አንዲሁም “አንዲህ አይነት ጥያቄ ካነሳህ እርምጃ ይወሰድብሃል” የሚሉ ንግግሮችን ተናገረውኝ አንጓጠውኛል በዚህም ምክንያት መመረቂያ ጽሁፌን ማስረከቤ ተሰናክሏል፡፡
- በምርመራ ወቅት በዙ አጻያፌ ስድቦችን እየተሰደብኩ የምመረመር ሲሆን ከነሱም መካከል “የነጭ ተላላኪ የነጭ አምላኪ አገር ሻጭ ከሃዲ “ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
- የዞን 9 አላማ ተናገር ካልሆነ ያሉንን የምርመራ መንገዶች ተጠቅመን እንድታወጣ እናደርጋለን የሚለው ማስፈራሪያ በተደጋጋሚ በምርመራ ወቅት የደረሰብኝ ነው
- የሰጠሁት ቃል ላይ እኔ ያላልኩትን ጨምረው በፍርሃት ጥፋተኛ ነኝ ብዬ አንድፈርም ከመገደዴም በላይ የበላይ አካል ተቀባይ አንዲሆን በሚል እየቀያየሩ በተደጋጋሚ አስፈርመውኛል፡፡
*ይህ ጽሁፍ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው